
የደንብ ቃላት መግለጫ
በከተማ ደንብ ማስከበርና በህዝብ ሪፖርት ላይ የሚያገለግሉ የቁልፍ ቃላት ትርጓሜ።
እነዚህ መግለጫዎች በከተማ አስተዳደር አካላት ደንብ በማስከበር ሥራ ውስጥ የሚታወቁ ቃላት እንዴት እንደሚወሰኑ ያብራራሉ። ሙሉ የሕጎች ጽሑፍ በ«ህጎች እና ደንቦች» ይገኛል።
በሕገ-ወጥ መንገድ መሬትን መያዝ ወይም መሬትን መውረር
ማለት የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣዉን አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ በመተላለፍ አግባብ ካለው የከተማው አስተዳደር አካል ፈቃድ ሳያገኝ መሬትን መያዝ ወይም መውረር ነው፤
ሕገ-ወጥ የመሬት ይዞታ ማስፋፋት
ማለት አግባብ ካለው የከተማው አስተዳደር አካል በሕጋዊ መንገድ ከተሰጠው ቦታ በተጨማሪነት አዋሳኙ የሆነዉን መሬት አስፋፍቶ መያዝ ነው፤
ሕገ-ወጥ ግንባታ
ማለት በሕገወጥ መንገድ መሬትን በመያዝ ወይም ሕገወጥ የመሬት ይዞታ በማስፋፋት በተያዘ ቦታ ወይም በሕጋዊ ይዞታ ላይ ያለ ግንባታ ፈቃድ በእንጨት፣ በፕላስቲክ፣ በሸራ፣ በብሎኬት፣ በብረት ወይም በማናቸዉም ቁሳቁስ ከላይኛዉ የመሬት ገጽታ በላይም ሆነ በታች የተገነባ ማንኛውም ግንባታ ሆኖ የመጠን፣ የቁስም ሆነ የዲዛይን ለዉጥ ያደረገ ሲሆን እድሳትንም ያካተተ ነው፤
መንገድ
ማለት በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ዋና መንገዶች፣ መለስተኛ መንገዶች፣ መጋቢ መንገዶች፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የመንደር መንገዶች፣ አደባባይ ወይም የአደባባይ ዙሪያዎች፣ የመንገድ አካፋይ ደሴቶች፣ በመንገድ ግራና ቀኝ ያሉ የእግረኛ ወይም የብስክሌት ማስተላለፊያዎች፣ የባቡር ሀዲዶች፣ ድልድይ ወይም የጎርፍ ማስወገጃ መስመሮችን ወይም በከተማው መሪ ኘላን መሠረት ለመንገድነት የተያዘን ቦታ ይጨምራል፤
ሕገ-ወጥ የመንገድ ላይ ንግድ
ማለት በከተማ አስተዳደሩ በተወሰኑ ቀን እና ሰዓት በመንገድ ላይ ለመነገድ ከተፈቀደባቸው መንገዶች ውጪ በሌላ በማንኛውም መንገድ ወይም ቦታ ላይ የሚካሄድ ማንኛውም የንግድ ሥራ ነው፤
በረንዳ ንግድ
ማለት ማንኛውም ሰው በህጋዊ መንገድ ለንግድ አገልግሎት ከተፈቀደለት ቦታ ውጪ አዋሳኝ በሆነ መንገዶች ወይም ቦታ ላይ የንግድ ተግባር ማከናወን ነው፡
ህገ-ወጥ የውጭ ማስታወቂያ
ማለት በመንገድ ላይ ባለ የትራፊክ መብራቶች፤ ምልክቶች፤ፖሎች በድልድች፤ በእግረኛ መከላከያ እና በሌሎች አጥሮች ያለፍቃድ ማንኛውንም የውጭ ማስታወቂያ፤ በራሪ ወረቀት፤ ብሮሸር መለጠፍ፤ ማንጠልጠል ወይም ማሰራጨትን የሚያጠቃልል ነው፤
ደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ
ደረቅ ቆሻሻ፦ ማለት ከመኖሪያ ቤት፣ ከንግድ፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከጋራዥ፣ ከመንገድ ፅዳት፣ ከግንባታ፣ ከግብርና፣ ከመሬት ቁፋሮ ወይም ከጠቅላላው የሕብረተሰቡ ሥራዎች ወይም በእንስሳት ምክንያት የሚፈጠር፣ ጠጣር ወይም ከፊል ጠጣር ቆሻሻ ነው። ፍሳሽ ቆሻሻ፦ ማለት ከመኖሪያ ቤት፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከጋራዥ፣ ከማንኛውም መንግሥታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚወጣ የልብስ፣ የምግብ እቃዎች፣ የመጠጥ ዕቃዎች እጣቢ፣ አተላ፣ አምቡላ፣ የመፀዳጃ ቤት ፈሳሽ፣ የእንስሳት ማደሪያ ፍሳሽ፣ መርዛማ ንጥረ ነገር ያዘለ ወይም ያላዘለ ፍሳሽ የመሳሰሉት ነው።
አዋኪ ድርጊት
"አዋኪ ድርጊት" ማለት በባለቤትነት፣ በተከራይነት፣ ወይም በማንኛውም መልኩ በይዞታነት በያዘው ቦታ ወይም ቤት ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደቱን በሚያውክ አኳኽን በትምህርት ቤት ዙሪያ እስከ 200 ሜትር መጠነ ዙሪያ ክልል ውስጥ ቁማር እንዲጫወቱበት ወይም እዲያጫውቱበት፣ የመኝታ ቤት ንግድ አገልግሎት መክፈት፣ ፊልም እና ቪዲዮ ማሳየት፣ የቀንም ሆነ የሌሊት ጭፈራ መፈጸም፣ ማንኛውንም አይነት የአልኮል መጠጥ መሸጥ እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል።